ኢትዮጵያ የአፍሪካን የንግድ ልውውጥና የምጣኔ ሃብት ውህደት የሚያፋጥኑ ተግባራትን ማከናወኗ የሚደነቅ ነው- የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን

ኢትዮጵያ የአፍሪካን የንግድ ልውውጥና የምጣኔ ሃብት ውህደት የሚያፋጥኑ ተግባራትን ማከናወኗ የሚደነቅ መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ ተናገሩ።

በአፍሪካ የንግድና የምጣኔ ሃብት ቁርኝት እንዲሁም የመሰረተ-ልማት ትስስርን በማፋጠን የአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ዕቅድን ማሳካት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ሆኗል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ፣ ኢጋድና በአጠቃላይ ከዓለም ጋር የንግድና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር ለማፋጠን እየሰራች መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአህጉሪቷና በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎትና ተደራሽነቱን በማስፋት የነበረውን ጉልህ ሚና አስታውሰው፤ በመሰረተ-ልማትና ሌሎችም መስኮች ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ትስስር እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ የአፍሪካን የንግድ ልውውጥና የምጣኔ ሃብት ውህደት የሚያፋጥኑ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኗን በአድናቆት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በስፋት በማምረት ወደ ሥራ ማስገባት ትልቅ ትኩረት ተደርጓል ያሉት ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊው አፍሪካ ለዚህ ጥሩ አቅምና በቂ ሃብት አላት ብለዋል።

ኢትዮጵያም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታት የወሰደቻቸው የፖሊሲ ማሻሻያ ለዘርፉ ልማት ጥሩ መሰረት የሚጥል ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በአውሮፓውያኑ 2025 የአህጉሪቷ የንግድ ትስስር 7 ነጥብ 7 ትሪሊየን ዶላር እንደሚሆን ሲገመት በ2050 ደግሞ 46 ትሪሊየን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በአፍሪካ በመሰረተ-ልማትና ምጣኔ ሃብት አህጉራዊ ውህደትን ማምጣት በአጀንዳ 2063 ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል።

ምንጭ :- ኢዜአ